ጂያንፍራንኮ ዞላ እ.ኤ.አ በጁላይ 5 1966 የተወለደ ጣሊያናዊ የእግር ኳስ አሰልጣኝ እና የቀድሞ እግር ኳስ ተጫዋች ሲሆን በዋናነት የፊት አጥቂ ሆኖ ተጫውቷል። በአሁኑ ጊዜ በ ሌጋ ፕሮ የጣሊያን ሴሪ-አ ሲ የእግር ኳስ ሊግ የሆነው በምክትል ፕሬዝዳንትነት በመምራት ላይ ይገኛል።
የተጫዋችነት ዘመኑን የመጀመርያ አስርት አመታትን በጣሊያን በመጫወት ያሳለፈ ሲሆን በተለይም ከናፖሊ ጋር በመሆን ከዲያጎ ማራዶና እና ኬሬካ ጋር የሴሪያን ዋንጫ ማንሳት የቻለ ተጫዋች ነው። በፓርማ ደግሞ የጣሊያን ሱፐር ካፕ እና የዩኤፋ ዋንጫን አሸንፏል። በኋላም ወደ እንግሊዙ ክለብ ቼልሲ ተዛወረ ፣ እዚያም በ1996–97 የውድድር ዘመን ባሳየው ድንቅ ብቃት በእግር ኳስ ጸሐፊዎች የአመቱ ምርጥ ተጫዋች ተብሎ ተመርጧል። በክለቡ ቆይታው የUEFA ካፕ አሸናፊዎች ዋንጫ፣ የUEFA ሱፐር ካፕ፣ ሁለት የኤፍኤ ካፕ፣ የሊግ ካፕ እና የኮሚኒቲ ሺልድ አሸናፊ ሆኗል። በቼልሲ ኤፍ.ሲ የምንግዜም ምርጥ ተጨዋቾች አንዱ ተብሎ ሚታሰበው ዞላ በ2003 የቼልሲ ምርጥ ተጫዋች ተብሎ ተመርጧል።