የክርስቲያኖ ሮናልዶ አልናስር ባለፈው ቅዳሜ አልታዎን 4-1 በማሸነፉ በጥሩ አቋሙ ሲቀጥል ክርስቲያኖ ሮናልዶ አንድ ግብ በማስቆጠር 2023ን 54 ጎሎች በማስቆጠር አንደኛ ሆኖ አጠናቋል።
ቀድሞውንም በ53 ጎሎች ኮከብ ጎል አግቢነቱን መምራቱን ያረጋገጠው ሮናልዶ ትላንትና 54ኛ ጎሉን በንጉስ አብዱላህ ስታዲየም በ92ኛው ደቂቃ ላይ በግንባሩ በመግጨት አስቆጥሯል። የ38 አመቱ ፖርቹጋላዊ የፊት አጥቂ ሃሪ ኬን እና ኪሊያን ምባፔ ሁለቱንም በ 2 ጎሎች በልጦ አጠናቋል።
ሮናልዶን በቅርብ ርቀት ሲፎካከር የነበረው ኤርሊንግ ሃላንድ በቅርቡ በእግር ላይ በደረሰበት ጉዳት ምክንያት ኖርዌያዊው የማንቸስተር ሲቲ አጥቂ 2023ን በ50 ጎሎች አጠናቋል።
ሮናልዶ በቅዳሜው ጨዋታ ያስቆጠራት ጎል በዚህ ሲዝን በ18 የሳዑዲ ፕሮ ሊግ ጨዋታዎች 20ኛው ጎሉ ሲሆን ወደ ክለቡ ካመራ በኋላ በሁሉም ውድድሮች ከ44 ጨዋታዎች 38 ጎሎች አስቆጥሯል።
2023 CR7 የዓለም እግር ኳስ ከፍተኛ ጎል አስቆጣሪ ሆኖ ሲያጠናቅቅ ለአምስተኛ ጊዜ ነው። ከዚህ ቀደም በሪያል ማድሪድ ቆይታው አራት ጊዜ ማሳካት ችሏል – በ2011 (60 ግቦች)፣ 2013 (63)፣ 2014 (61) እና 2015 (57)።